ሃገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሃገር ቤት የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች አዲስ አበባ ፍፁም ሰላም የሰፈነባት ከተማ መሆኗን ማረጋገጣቸውን ተናገሩ፡፡በመላው ሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
*******
ኢትዮጵያ ተጣርታ አልቀርም በማለት ኑሯቸውን በተለያዩ ሃገራት ያደረጉ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሃገር ቤት በመግባት ላይ ናቸው፡፡
የዲያስፖራው ማህበረሰብ በቃ ወይም # NO MORE በሚል ጠንካራና ተከታታይ ሰልፍ በማድረግ የኢትዮጵያ ልሳን በመሆን የሀገራቸውን ድምፅ ሲያሰሙ መቆየታቸው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ እንድሪስ መሃመድ በተለይ ለአዲስ ፖሊስ ገልፀዋል፡፡ ማህበራቸው ልዩ ልዩ ሃገራዊ ጉዳዮችን በማስተባበር በውጪ የሚገኙ ዜጎች ለሃገራቸው እድገት እና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአውሮፓ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን አሻግሬ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ሃገራችንን ያጋጠማትን ችግር ለመቅረፍ መላው ህዝብ እየተረባረበ እንደሆነና የዲያስፖራው ማህበረሰብም የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን በማስታወስ አሁን የተጀመረው የሃገርን ጥቅም የማስጠበቅ እንቅስቃሴን አጠናክረን በመቀጠል የሃገራችንን ችግር በዘላቂነት ልንፈታ ይገባል ብለዋል፡፡
ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ሚኒሶታ የሆነው ወ/ሮ ዘኒ ተሾመ ሃገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት እንደመጡና እየተደረገ ባለው አቀባበል በጣም መደሰታቸውን አስረድተው ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ በመሆኑ የገና በዓልን ለማክበር ወደ ላሊበላ ለመሄድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የመምጣታቸው ዋነኛ ምክንያት ስለ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት የሚነገረውን የተዛባ መረጃ ሃሰት መሆኑን ለመላው ዓለም ለማሳወቅና ለሃገራቸው እና ለወገናቸው ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት እንደሆነ ከአዲስ ፖሊስ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት ሃሳባቸውን አጋርተውን ይህን በማድረጋቸውም ሀገራዊ ኩራት እንደተሰማቸው እንግዶቹ ገልፀዋል፡፡
የዲያስፖራ አባላቱ በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው ከተማችን አዲስ አበባ ፍፁም ሰላም የሰፈነባት እንደሆነች በተለያዩ ስፍራዎች ተዘዋውረው ማረጋገጣቸው አስታውቀው በመላው ሀገራችን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለገና በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለመላው አመራሮችና አባላት በሦስት ዙር የሠጠውን የአቅም ግንባታ ስልጠና አጠናቀቀ፡፡ ወቅቱ የሚጠይቀውን ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ተቋሙን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው ገልፀዋል፡፡
በኮሚሽኑ ከመጋቢት 9 እስከ ሚያዚያ 9 ቀን 2011 ዓ/ም በሦስት ዙር ለመላው አመራሮችና አባላት የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ሚያዚያ 10 ቀን 2011 ዓ/ም በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት የፀጥታ አካላትን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘው ሀገራችን በለውጥ ጎዳና ላይ እንደምትገኝድ እና ለውጡ ህዝባዊና ህገ-መንግስታዊ መሆኑን በመጥቀስ በህዝብ ፍላጎት የመጣው ለውጥ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የፀጥታ አካላት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
ለውጡ በፖሊስ ተቋማት ውስጥ ስኬታማ እንዲሆን እና ወቅቱ የሚጠይቀውን ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ተቋሙን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን የጠቁሙት ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከምንም በላይ ለሰው ሀብት ልማት እና ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የፖሊስ አመራሮችና አባላት የለውጡን ባህሪ ተገንዝበው በተለይ ሰብዊ መብቶችን አክብረው በማስከበር ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ህዝብና መንግስት ቅን አገልጋይ እንደሚፈልጉ ተናግረው ኮሚሽኑ የለውጡ አካል በመሆን ህዝባዊና ዲሞክራሲያዊ የፖሊስ ተቋም በመገንባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገችና እየዘመነች ለምትገኘው ከተማችን የሚመጥን የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ስልጠናው የአመራሮችን እና የአባላትን የማስፈፀም አቅም ለማጎልበት የራሱ ጠቀሜታ ማበርከቱን ኮሚሽነር ጌቱ በንግግራቸው ጠቁመው መሰል ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በቅርበት ከሚሰሩ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎ ሺፕ ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ ልዩ ልዩ መልክቶችን ያስተላለፉ ሲሆን ተቋማቸው ለፀጥታ አካላት የሚሰጠውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡በአስራ ሦስት የተለያዩ ስፍራዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተደግፎ በተሰጠው ስልጠና ላይ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ስልጠናውን ተከታትለውታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት የሰላም ፤ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የሌሎች አስፈፃሚ አካላትን የ2011 በጀት ዓመት በ9 ወር የተከናወኑ የፀጥታማስከበርስራዎችን በጋራ ገምግመዋል፡፡በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሚያዚያ 10 ቀን 2011 ዓ.ም የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የተከበሩ አቶ ኤፍሬም ግዛው የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት የሰላም ፡ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፤ እና ሌሎች የም/ቤቱ አባላት፤የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ፤ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፤የሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና ከደንብ ማስከበር ዘርፍ የተውጣጡ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊሰ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በመዲናችን ወንጀልን እና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እንዲሁም የተጀመረውን ሃገራዊ ለውጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የኮሚሽኑ አባላትና አመራር ልዩ ትኩረት ሰጥተው ለህብረተሰቡ ስጋት የሆኑ ወንጀሎችን ለመቀነስእየሰሩ መሆኑን ገልፀው ፡ ከሪፖርቱ የተገኙ መልካም አፈፃፀሞችን በማጠናከርና የታዩ ክፍተቶችን በማረም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በቀጣይ ከከተማው ማህበረሰብ፤ከአስፈፀሚና ከአስተዳደር አካለትጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩ በመጠቆም የህ/ቡ እና የተቋማት ድጋፍና አጋርነት ወሳኝ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት የሰላም፤ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ኤፍሬም ግዛው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከተማውን ሁለንተናዊ ሰላም በማስፈን በርካታ የሚታዩና የሚለኩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡በቀጣይ በጋራ በመተባበር የተጀመረውን ለውጥ እንዳይደናቀፍ ማስቀጠል፤የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት፤የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ እና ሌሎች መልካም ተግባራት በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ከመድረክ ለተነሱ ጥያቄዎችም በከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
በዕለቱ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የዕቅድና በጀት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ማሞ የአስፈፃሚ ተቋማት በጋራ ለመስራት ያቀዱትን የህዝብ ስራ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ እና ያለ ህዝብ ትስስር የሚሰራ ስራ ውጤቱ አርኪ ስለማይሆን ከምንም በላይ የህ/ቡ ተሳትፎ ማደግ አለበት ብለዋል፡፡
ለጥቁር ገበያ ለሽያጭ ሊቀርብ የነበረ ነዳጅ እና ግምቱ ከ1ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ ከህብረተሰብ በደረሰ ጥቆማ መያዙን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው በተለምዶ 7ኛ ሸንኮራ በረንዳ ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ ከሚገኘው «ትዕግስት ብሩክ ቶታል ማደያ»ውስጥ ጥር 12 ቀን 2011 ዓ/ም የተቋሙ ሰራተኞች ከህገ-ወጦች ጋር በመተባበር በ44 ጀሪካን 995 ሊትር ቤንዚን ከማደያው በመቅዳት ላይ እንዳሉ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የተቀዳውን ቤንዚን እና ሌላ ሊቀዳበት የነበረ 44 ባዶ ጀሪካን እንዲሁም የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 አ/አ 29642 አይሱዙ ተሽከርካሪን ከአምስት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ኃላፊ ኮማንደር ጌታነህ በቀለ ገልፃዋል፡፡
የማደያው ሰራተኞች ቤንዚን በጥቁር ገበያ ከሚሸጡ ህገ-ወጦች ጋር በመተባበር ድርጊቱን መፈፀማቸውን ፖሊስ በምርመራው ማረጋገጡን ፤ በህገ-ወጥ ተግባሩ ላይ ተሳትፎ ያደረጉ አምስት ግለሰቦች ምርመራ እየተጠራባቸው እንደሚገኝ ኮማንደር ጌታነህ አስረድተዋል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋለው ቤንዚን ከ11 ሺ ብር በላይ ዋጋ እንደሚያወጣ ኃላፊው ተናግረው በልዩ ልዩ ጊዜያት ግምቱ 38 ሺ ብር በላይ የሚያወጣ 112 ጀሪካን ቤንዚን ተይዞ ምርመራው ተጣርቶ የምርመራ መዝገቡ ለዓቃቤ ህግ መላኩን ከኮማንደሩ ገለፃ መረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ/ም ልዩ ቦታው አማኑኤል ቤተ-ክርስቲያ አካባቢ ኮድ 3-47453 አ/አ የሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ከላይ ሲሚንቶ በማድረግ ከስር 63 ጀሪካን ቤንዚን ጭኖ ሲንቀሳቀስ በድንገተኛ ፍተሻ መያዙን ኮማንደሩ አስረድተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ጥር 13 ቀን 2011 ዓ/ም ምዕራብ ሆቴል አከባቢ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 80502 አ/አ የሆነ ተሽከርካሪ ግምቱ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ በኮንትሮ ባንድ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ልዩ ልዩ እቃዎች ይዞ ሲንቀሳቀስ ፖሊስ መምሪያው ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ተሽከርካሪውን መያዙን ነገር ግን አሽከርካሪውን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆንን ኮማንደር ጌታነህ ገልፃዋል፡፡
ተሽከርካሪው በብርቱ ክትትል ሲያዝ በርከታ ጣቃ ጨርቆች ፣ 2ሺ የሞባይል ቻርጀሮች ፣ 3480 አይነቱ «ኑር ሴላ»የሆነ ሲጋራ እና 1ሺ የሪሲቨር ሪሞት ኮንትሮል ይዞ ለማለጥ ሲሞክር እንደተያዘ ሀላፊው አስረድተዋል፡፡
መርካቶ የንግድ ስፍራ በመሆኑ በተለይ የኮንትሮ ባንድ ንግድ እንደሚስተዋል እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቤንዚን በጥቁር ገበያ ለመሸጥ እንቅስቃሴ መኖሩን ነገር ግን ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሚሰጠው ጥቆማ አብዛኞቹ እየተያዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ህገ-ወጥነትን በጋራ መከላከል የሚቻለው ህዝብና ፖሊስ በጋራ ሲጣመሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልፆ ህዝቡ ጥቆማ በመስጠትና አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ምስክር በመሆን እያረገ ያለውን የነቃ ተሳትፎ አጠናከሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ኮሚሽኑ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡